እንደመታደል ታሪክ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን እንዲያደላ ይገደዳል። በታላቁ መፅሐፍ የኢትዮጵያን ምድር ይከብ ዘንድ የታዘዘው የዓባይ ወንዝ የሚያጋምዳቸው ግብፅና የእኛ አገር ኢትዮጵያም በየ ታሪክ አውዱ ሲመዘኑ የአበሾቹ አገር ሚዛን ትደፋለች።
ያኔ ዓለም እንቅልፉን እየለጠጠ ነው። የአፍሪካ ከዋከብቱ ኢትዮጵያና ግብፅ ግን የስልጣኔ ብርሃን እየፈነጠቁ ነበር።ከሁለቱ ሃያላንም ገዥና ተገዥ አስፈለገ።
የዓባይ መነሻዋ ኢትዮጵያ ፍጥጫውን አሸነፈች። በተለያዩ ጊዚያትም በፈረኦን የምትተዳደረውን አገረ ምስር ወይም ግብፅ በጥቋቁር ነገስታቷ መራቻት።
ጋዜጠኛና ደራሲ ፍስሃ ያዜ ካሳ “የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ”በሚለው ሸጋ መፅሐፉ እንዲህ ይለናል፦
“18 ኢትዮጵያዊ ነገስታት ግብፅን ገዝተዋል።”
ድሃ ህዝብ በመሆናችን የሚናገርልን ስለሌለን እንጅ ኢትዮጵያዊያን ዓለምን ቀድመን የሠለጠን እንደነበርን በተባራሪ የሚወጡ ፈረንጆቹ የደበቁብን የታሪክ ማስረጃዎች ያስረግጣሉ።
ስለ ስልጣኔ ጀማሪነት ሲነሳ ልትወዳደረን ከቻለች ሁለተኛ የምትወጣው አገር ግብፅ ብቻ ናት። የሁለተኛነቷንም ምክንያት ዲሞክሪተስ የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ እና ተመራማሪ በአንድ የምርምር ስራው ላይ”ኢትዮጵያዊያን የስልጣኔ እርሾ ስለሰጧቸው ግብፃዊያን የኢትዮጵያዊያን ውለታ አለባቸው።”ያለበትን ፅሁፍ ፍስሃ ያዜ ካሳ እና ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ በየመፅሐፋቸው ውስጥ አካተውታል።
የቀደሙት ጥቁር የኩሽ ሕዝቦች ከሚታየው ከሚዳሰሰው አስደማሚ የሰው ልጅ ስልጣኔ አለፍ ብለው በመንፈሳዊና የፍልስፍና ልህቀት ላይ ሲራቀቁም ለተዓምር የቀረበ ተመስጦን የተቸሩ ፍጡራን እንደነበሩ የሚያመለክተው አሳንቴ የሚባል ፀሐፊ ከዚህ ቀጥሎ የገለፀው ሃቅ ነው።
“የኢትዮጵያዊያን ሰዎች” ይላል አሳንቴ “የኢትዮጵያዊያን ሰዎች ታላቅ እውቀት ባለቤት መሆናቸውን ግብፃዊያን እንደሚያደንቁት ሁሉ ግብፃዊያን ሰዎች ያላቸውን ታላቅ የሆነ ክህሎትና እውቀት ማንም ግሪካዊ ያደንቅ ነበር።”
ነገሩ ወዲህ ነው። እውቀትና ጥበብ እንደ ግዮን ውሃ ከኢትዮጵያ ከፍታዎች እየፈለቀች ወደ ግብፆች ትፈስና ባህር አቋርጣ ግሪክ ትደርስ ነበር።
የኩሽ ልጆች ልዕልና ያልተነገረለት እንቁ የታሪክ ክታብ ነው።ኢትዮጵያዊያን የግብፅን 25ኛ ስርዎ መንግስት ስለመመስረታቸው ታሪክ ሊፅፉ ብዕር ባነሱ ሰዎች ሁሉ ተከትቧል።ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን ያደላል።ኢትዮጵያ የስልጣኔ መምህር ነበረች ይላል።
እንግዲህ ምን ይደረግ? ፍሬደሪክ ቦልተን Plant and Planiet ሲል ባቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ውስጥ ጥቁሩን ኢትዮጵያዊ ግስላ”የዓለም የድንጋይ ዘመን ብቻም አይደለም:፤የሁሉም ቀደምት ስልጣኔ ብርሃን ፈንጣቂ ህዝቦች ጥቁር ኑብያንስ ናቸው።” በማለት የዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊያንን ያሞካሻቸዋል።
Picture: Ethiopia and the Origin of Civilization
ስለ ግብፅና ኢትዮጵያ የአነሳስ ታሪክ እንዲህ ከተንደረደርን አሁን ደግሞ ባይዋደዱም በግድ ስለገመዳቸው የዓባይ ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ሸለቆው እንውረድ፦
እንግዲህ ከተሜም ሆንን ገጠሬ ስለ ግብርና ሙያና አሰራሩ ትንሽ መባባል አለብን።በገጠር በተቻለው መጠን ገበሬው ቤቱን የሚሰራው ከፍ ያለ ቦታ ፈልጎ ነው።ከዚያ ከተራራው እየወረደ አዝዕርቱን ይዘራና አርሞ፣ኮትክቶ–ሲያፈራለት ያጭዳል—የቀደሙት የኩሽ ኢትዮጵያዊያንም ከዛሬ አምስት ሺህ ዓመት በፊት አገራቸውን ኢትዮጵያን ቤት መስሪያቸው አድርገው፤ ግብፅን እህል መዝሪያቸው—ገባሪያቸው እንደነበረች ፍስሃ ያዜ ካሳ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህኣዴግ” በሚለው 72 መፅሐፍትን ያጣቀሰ ማራኪ ስራው ሲያትት—
“የመጀመሪያው ግብር ታችኞቹን(ግብፆቹን ነው) ላይኞቹ(ኑብያን) አስገባሪ ሆነው የተጀመረው በዚያን ጊዜ ይመስላል። የኑብያ ኢትዮጵያዊያን ወረድ እያሉ ምርታቸውን ያዩ እንደነበር በብዙ ተፅፏል።” እያለ ነው
እዚሁ ላይ በጉልህ የተገለፀው ሌላ ነገር ሁለቱን የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አገራት ድብብቆሽ ሲያጫውታቸው የኖረውና ዛሬም ያለው እስከ ምፃቱ ቀን ሊቀጥል የሚችለው ዓባይ በዚያን የኢትዮጵያዊያን አስገባሪነት ጊዜ ለሁለቱም አገራት የጋራ ጣኦት የነበረ መሆኑ ነው።ፍስሃ ያዜ ካሳ እንደፃፈው”—ኒል(ዓባይ) የጋራ አምላካቸው እንዲሆን ተስማምተው ነበር ይባላል።”
ካነሳነው አይቀር በታሪክ አጋጣሚ ሱዳን የሚባል አገር የተወለደው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው።እንደ ረጅሙ ወንዝ ዓባይ በሚጥመለመለው የኢትዮጵያዊያን ትዕንግርት መሰል ታሪክ ውስጥ ኑብያን እንጅ ሱዳንን አለች የሚል ሰነድ የለም።ኢትዮጵያ እና ኑብያ ማለት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ እንደማለት ነው። ኢትዮጵያ የኑብያ ባለቤት ስትሆን የግብፅ አድራጊ ፈጣሪም ነበረች።
አሮጌው ስልጣኔ ተደጋግሞ እንደሚገለፀው ዓባይን ይመስል ከኢትዮጵያ እየመነጨ ወደ ግብፅ ሲፈስ ኖሯል።
ኢትዮጵያዊያን የስልጣኔ ማማ ላይ ሳሉ አሁን ለሰሚው ግራ የሚመስሉ አስደናቂ ስራዎችን በዚያ ምድር ፈፅመዋል።
ሁለቱም የአፍሪካ ባልቴቶች ግብፅና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸው ከታላቁ የግዮን(ዓባይ) ወንዝ አንፃር ተመዝኖ ሲጓዝ እነሆ 7512 ዓመታትን አሳልፏል።
አብዛኛውን ጊዚያቸውን አዲስ አበባ ራስጌ እንጦጦ ተራራ ላይ እንዳሳለፉ የሚነገርላቸው ዓፄ ዳዊትና ግብፅ ዓይን እና ናጫ እንደነበሩ ታሪክ በደማቁ የፃፈው ሲሆን ዋንኛው የግጭታቸው መንስኤ የግብፅ ሱልጣኖች ወደ ኢትዮጵያ በሚልኳቸው ሊቀ-ጳጳሳት ከሚያገኙት ከፍተኛ ግብር መዋዠቅ ጋር የተያያዘ እንደነበር ፍስሃ ያዜ ካሳ ይገልፃል።
ከአፄ ዳዊት በሗላ የሶሎሞናዊው ስርወ መንግስት አለቃ ሆኖ በኢትዮጵያ ምድር የነገሰው አፄ ሰይፈ አርዕድም ወደ ላዕላይ ግብፅ ዘምቶ አሳሪዎቻቸውን አፈር ድሜ በማስጋጥ በዚያ የታሰሩ ኢትዮጵያዊያንን አስፈትቷል።
አረቢኛን ቀድመው ተምረው አረብን አላምንም ይሉ የነበሩት-ቋረኛው ካሳ—አጤ ቴዎድሮስ ከሞታቸው በፊት የቀመሷት የመጀመሪያ ሽንፈታቸው ከግብፆች ጋር ደባርቂ የምትባል የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ያለች የጦር ሜዳ ናት።
የታጠቅ ጌታ—አጤ ቴዎድሮስ ከግብፅ በቀመሷት ሽንፈት ተነስተው ኢትዮጵያን በጦርም በሌላ ነገርም ለማዘመን ላይ ታች ሲሉ ከሚበጠብጧቸው የቤተ-ክርስትያን ሰዎች መካከል ከግብፅ የመጣው አቡነ ሰላማ የሚባል ጳጳስ ነበር።ቆፍጣናው ንጉስ አጤ ቴዎድሮስ ይሄንን ቀላል ጳጳስ”ከሴቶች ጋር በስውር ሲወሰልት አይቸዋለሁ” ብለው ሲያዋርዱት እሱም አለኝ በሚለው የመራገምና የመመረቅ ስልጣን እንዲህ ሲል ረገማቸው ይለናል—ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪው ፍስሃ ያዜ ካሳ በ”የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህኣዴግ” መፅሐፉ፦
“ልዑል እግዚያብሔር በሚያመጣው መቅሰፍት ይቅሰፍህ፣ከከዳተኛው ይሁዳ ጋር እድል ፈንታህ ይሁን!”
ይህንን በኃይማኖት አሳቦ አገር ሊያተራምስ የመጣ የግብፅ ስመ ጳጳስ እንግሊዛዊው ሆርሙዝ ራሳም ባስተዋለው መሠረት ሲገልፀው፦”ጳጳሱ ተንኮለኛ፣አወናባጅ፣የሐይማኖት ጉዳዮችን እየተወ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የሚያውክ ጠማማ ሰውና ለገንዘብ ሲል ተገዝቶ የመጣ ተራ ባሪያ ነበር።” እያለ ነው።
“ትንሽ እልፍ ሲሉ እልፍ እየተገኘ
ድሃ ነው በልቡ ሞቱን የተመኘ”
እንዲል ማዲንጎ አፈወርቅ ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል።በዘመናት የዓለም ታሪክና ካርታ ውስጥ ያልነበረችው ሱዳን እንኳን እናቷን ኢትዮጵያን ወራታለች።
ታሪክ ራሱን እንደደገመ አለ።ያኔ በዝብዝ ካሳ አፄ ዮሐንስ ግብፃዊያንን ጉንደትና ጉራ በሚባሉ የጦር አውዶች በረመረሙበት አፍታ የሱዳን መሃዲስቶች ኢትዮጵያን እስከ ጎንደር ወርረው የማይደረግ አድርገው ነበር።የንጉሱም የዙፋንና የምድር ቆይታ ያከተመው በዚያ አጋጣሚ ነው።
አይበልባቸውና መራሄ መንግስት ዐቢይ አህመድም ከዚያ የ19ነኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ንጉስ ጋር ብዙ ጠባይ ይጋራሉ።
“የሰይጣን ጆሮ መደፈን”ያለበት ስለ አፄ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ ስናስብ ነው።የተቀረውን ሸገጋ ታሪክ መጋራት ለአሁኑ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ሆነ መራሄ መንግስት ጸጋ ነው።
ለሁሉም ታሪክ ራሱን ደግሟል።ሱዳን የኢትዮጵያን ውጥረት አስልታ ድንበር ተሻግራለች።
ያኔ 18 እና ከዚያ በላይ ጥቋቁር ፈረኦኖች ግብፅን ሲያስገብሩ ሱዳን መሸጋገሪያ ነበረች፤ንግስተ ሳዕባም ወደ ጠቢቡ ሰለሞን ስትሄድ በኑብያ ምድር እህል አያስዘራች ውላም እያደረች ነበር።
ዛሬ ኢትዮጵያ የምትመካው በታሪኳ ብቻ ከሆነ ያሳዝናል። ያለንበት አፍታ ተስፋ እና ጨለማ የተፋጠጡበት ይመስላል።ተስፋ ካሸነፈ ዳግም ዓለምን እነመራለን፤ወደ ጨለማው ከገባን የታሪክን ዶሴ ታቅፈን እንቀራለን።
ይቆየን!
Article By: Tamene Mengste