መቼም ሰሞነ አድዋ ላይ ነንና ሬዲዮዎው ስለ አድዋ ታሪክ ይተርካል ቴሌቭዥኑ አድዋን ሊያሳይ ይታትራል ወጣ ብለህ አየሩን ብትምግ አየሩ አድዋ አድዋን ይሸታል የሰሞነ አድዋን ውሀ ብትቀምስ ውሀው ውስጥህ ሲንቆረቆር ዘራፍ እኔ ወንዱ ወግድ ዘረኝነት ወግድ ጎጠኝነች ያሰኛል።
እኔም የሰሞነ አድዋን አየር ምጌ ውሀውን ቀምሼ ስለ ሰሞነ አድዋ ልፅፍ ብእሬን ከወረቀቴ ጋር አዋደድኩ። አድዋንም አናግራት ቀጠልኩ ተናገሪ አድዋ ብዬ ብጠይቃት ስለ ጀግኖቹዋ በእምባ አወጋችኝ።
ትናገር አድዋ ፤ ትናገር ትመስክር
በማለት የአድዋን ፤ ታሪክ ብንተረትር
በእምባ በሲቃ ፤ ትናገራለች አድዋ
ደም ለሞዠቁላት ፤ ለህያው ልጆችዋ
ህይወት ለለገሱዋት ፤ ለውድ አርበኞቹዋ
እቺን ግጥም ጭሬ አድዋ ካወሳችኝ ጀግኖቹዋ መሀል አድዋን ዛሬ እንድንፅፍ አድዋን ዛሬ እንድናነብ አድዋን ዛሬ እንድንሞዝቅ አድዋን ዛሬ እንድንስል ሰው ሆነን ስንፈጠር ከሰውነት ጋር የተለገሰንን ነፃነት እንዳንቀማ የመቀማቱን ምስጢር በጣልያነኛ ከተፃፈው የውጫሌ ውል አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ የተባሉ የቋንቋ ሊቅ በአፄ ምኒሊክ አዛዥነት ተርጉመው ይህ ውል ነጣነታችንን አሳልፎ የሚሰጥ ውል ነው በማለታቸው በአፄ ምኒሊክ በታሰሩ ጊዜ ስለ አፅመ ጊዮርጊስ ልክነት በመመስከር ለእውነት በእውነት ስለሚሞግቱት የኢትዮጵያ ዱኛ ተሟጋች ስለሆኑት ስለ ብርሀነ ዘ ኢትዮጵያ መፃፍን መረጥኩ።
አድዋ ያወሳችኝ በእምባዋ የተረከችልኝ ብዙ ጀግኖች ቢኖሩም ለዛሬ ብርሀነ ዘኢትዮጵያን መርጫለሁ።ብርሀነ ዘ ኢትዮጵያ ማነው ብላቹ ትጠይቁ ይሆናል እኔም ስለ እሳቸው ለመመለስ ሳላቅማማ ታሪካቸውን በጥቂቱ እንካቹ ልበላቹ።
ብርሀነ ዘኢትዮጵያ ስል ይህ ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ አንድ ሪዙን ያዥጎረጎረ ፀጉሩን ያጎፈረ የሚሸልል ታላቅ አባት ያስብ ይሆናል። ነገር ግን ብርሀነ ዘ ኢትዮጵያ ጀግንነት እና የዋህነት ጭካኔን እና አዛኝነት የጦር አዛዥነት እና እናትነት ያሰናሰሉት ከባለ ብዙ ታሪክ ባለቤት ከሆነችው ከደቡብ ጎንደር በጌምድር ከደብረ ታቦር ከተማ የበቀሉት እቴጌ ጣይቱ ናቸው።
አፄ ምኒሊክ ከነገሱ በ አስራ ሁለት አመታቸው ፋሲካን ለማክበር ሱሉልታ አካባቢ ሄደው የጣይቱ እናት ቤት ደብረ መይ ጎራ ባሉ ጊዜ አንዲት ቆንጆ ወጣት አዩ ሳያንገራግሩም እቺ ሴት ሚሽቴ ናት ብለው አጩዋት ያቺ ሴትም የደጃዝማች ብጡል ልጅ የሆነችው ጣይቱ ነበረች።
ከሁለት አመት በዋላ ወደ ንጉሱ መኖርያ ጎጃም እንድትመጣ ተደርጎ በታጩበት ተመሳሳይ በአል ፋሲካ በአንኮበር መድሀኔአለም ቤተክርስትያን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተጋቡ ከልጅነት ጀምሮ ሲመኟት እንደ ህልም ሲያልሙዋት የነበረች ፀሀይቱ እጣይቱ ተብሎ ተፃፈላት።
ወደ አድዋ ታሪክ ልመለስ እና በስህተት የታሰሩትን አፅመ ጊዮርጊስን አስፈትተው እንዲ ሲሉ ዮሴፍን ወቀሱ።ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዮሴፍ ፣ ጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳይስጠነቅቅዎ ቀረ?» በማለት ዮሴፍን ጠምደው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዮችን ሁሉ እሳቸው ሳያዩት እንዳያልፍ ተደረገ።
እያንዳንዱ ሰው ስለተነሳው ችግር ያለውን አስተያየት ሀገር ፍቅር በተሞላበት አንደበትና የጋለ መንፈስ ሲገለፅ ከቆየ በኋላ። የሀገር ፀሀይ የሆነችው እጠሀይቱ ዛሬ የምንዘምርለትን አድዋ እንዲ ሲሉ አስጀመሩት «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» በማለት ህዝቡን በተለያየ ቃላት አነቃቁት እሳቸው እናት ነበሩ እሳቸው ጨካኝም ነበሩ እሳቸው ፖለቲከኛ ነበሩ እሳቸው አነቃቂም ነበሩ እሳቸው ብልህ ነበሩ ብዙ ማለት ቢቻልም አጠር ባለች ስንኝ ፅሁፌን ልዛዝማት።
ያቺ እቴጌይቱ ፤ የነፃነት ፀሀይ
ብርሀነ ኢትዮጵያ ፤ ባርነት እንዳላይ
በማለት ሞገቱ ፤ ምስጢሩን አጤኑ
ዮሴፍን ጠማምደው ፤ አፅመን አዳኑ
ቃላትን ቀጣጥለው ፤ ህዝብን አጀገኑ
ፀሀፊ ናትናኤል ወጋየሁ