“.…ሰላም ፍቅር ጤና ለኛ
ድንቅ ብርቅ በአለም እኛ
እውነት እውነት እሷም ለኛ
እናት ሀገር ትኑር ለኛ
እናት ሀገር ትኑር ለኛ…”
እያልኩ የካስማሰን ዘፈን እያንጎራጎርኩ ልክ እንደ እሱ በቄንጥ ከወገቤ አጎንብሼ እጅ በመንሳት የተከበረ ሰላምታዬን አቀረብኩላችሁ።ሰላም ፍቅር ጤና ለኛ።
ያው እንደለመደብኝ ዛሬም ስለ አድዋ ድል ላወራችሁ ፈለግሁ። አይሰለቻችሁም ብዬ ተስፋ አደርጋለው። አውቃለው ስለ አድዋ ድል ብዙ ተብሎለታል፤ተወርቶለታል፤ተዘምሮለታል፤ተዘክሮለታል አሁንም ቢሆን እየተባለለለት ይገኛል። ግን አብዛኛው እኛው ስለራሳችን ያወራነው ነው ፤ ከአባቶቻችን የሰማነው፣ከታሪክ መፅሀፎቻችን ያነበብነው በእኛ ወገን ያለ የድል ገድል ነው። ከእነሱን አልሰማንም፤ ብዙም የመስማት እድሉንም አላገኘንም። የሽንፈት ፅዋ ቀማሾቹ ጣሊያኖች የአድዋን ጦርነት እንዴት ይገልፁታል? የዛሬ ፅሁፌ ሚያተኩረው እዚህ ላይ ነው። “ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ” ከተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መፅሀፍ የቃረምኩትን ጀባ ልላችሁ ፈለግኩ። መልካም ንባብ።
“…የተተከለው ድንኳን ሲታይ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ ኤሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል ። የጦርነቱ እለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው ፥ ጠመንጃና ጦር ይዘው ፥ ጎራዴ ታጥቀው ፥ የነብርና ያንበሳ ቆዳ ለብሰው ፣ አዝማሪዎቹ እየዘፈኑ ፣ ቄሶች ፥ ልጆች ፥ ሴቶች ሳይቀሩ ፀሀይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያን ጦር አሸበሩት ። …” በርክለይ
“…ውጊያው እስቲጀመር እንጠብቃለን ። … እህቴ ሆይ ፥ ይህ ደብዳቤ ሲደርስሽ በህይወት እንደሌለሁ ቁጠሪው ። በህይወት የምትቀሪው አንቺ እህቴ ለታዘዝኩበት ስራ በክብር መሞቴንና በክብር መሞት ደግሞ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን መስክሪ ። …” ካፒቴን ካኖቫቱ ለእህቱ ከፃፈው ደብዳቤ ላ.ጉየራ ኢን አፍሪካ ከሚለው መፅሀፍ
“… በእንዲህ አይነት የጭንቅ ጊዜ መልካም ምኞቴን ልገልፅልህ እወዳለሁ። … ጥቂት ሰዓት ከሚያስኬድ ርቀት ላይ ራሶች ተሰልፈዋል ። ባንድነት ወደኛ ይጓዛሉ ። ባታሊዮናችንም እንድናፈገፍግ ብቻ ይነግረናል ። የዚህ ውጤት መጨረሻ ምን እንደሚሆን ይገባሀል ። ጦሩ እየገፋ እስቲመጣ ድረስ ብቻ እንጠባበቃለን ። … ለታዘዝነው ትዕዛዝ ህይወታችንን እንሰዋለን ። የኛ ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ። አሁን ሁሉንም ነገር ትቼ የማስበው ለተከበረው ሽማግሌ አባቴና ለተከበረች እናቴ ነው ። አንድ የምለምንህ ነገር አለኝ ። ቤተሰቦቼን ምንም ነገር ቢያገኛቸው እንድትረዳቸው አደራ እእልሀለው ። … ” መቶ አለቃ ሚሴና ፥ ላ.ጉየራ ኢን አፍሪካ ከሚለው መፅሀፍ
በጦርነቱ ጊዜ በኢጣሊያ አገር በሚላኖ ለሚገኙ ጋዜጦች ሁሉ ተወካይ ሆኖ የመጣው አኪሊ ቢዞኒ አገሩ ከተመለሰ በኃላ ሲ.ኤርት ሪያ ኔል .ፓሳቶ.ኢ.ኔል ፕሬዜንቱ በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሀፉ ውስጥ ሲገልፅ “… ከጧቱ 2 ሰዓት ተኩል ሲሆን ሰራዊቱ በሙሉ ቦታውን እየለቀቀ ሸሸ ። አባ ገሪማና አባ ሹለዳ በጠላት እጅ ወደቁ ። ጠላት በመስመር ፥ በመስመር እየሆነ ይመጣብን ጀመር ። በአከባቢው የነበሩ 14 መድፎቻችን እያጣደፉ ይተኩሱ ነበር ። ጀነራል አልቤርቶኒ ማጥቃቱን ትቶ ወታደሩ ለራሱ እንዲከላከል ትዕዛዝ ሰጠ ። የጠላት ጦር ግን የማይቻል ሆኖ መጣብን ። ንጉሱም ቀይ ጃንጥላቸውን አስይዘው በወታደሩ መሀል ነበሩ ። …ጠቅላላ መድፎቻችንና መትረየስ ተኳሾቻችን ባላቸው ሀይል ሁሉ በየማዕዘኑ ይተኩሱ ጀመር ። … 6ኛውና 8ኛው ባታሊዮን ከቀኝና ከፊትለፊት ከሚተኮሰው የጠላት ጥይት ከባድ ጉዳት ደረሰበት።
“… የጀነራል አልቤርቶኒ ወታደሮች በሙሉ ተያዙ ። ጠላትም ያን ቦታ አልፎ ወደ ፊት ገሰገሰ ። 3 ሰዓት ተኩል ሲሆን ሁሉም ተስፋ ቆረጠ ። የቀረን የምንተማመንበት አንደኛ ባታሊዮን ብቻ ነው ። እሱም በእንዳ ኪዳነ ምህረት ላይ ባደረገው ግጥሚያ ብዙ መኮንኖች አለቁበት ። ይህ አንደኛ ባታሊዮን ከሌላ ባታሊዮን በተውጣጡ ወታደሮች ተሞላ ። ወዲያውኑ የጠላት የሀበሻ ወታደሮች ደርሰው ያባርሩት ጀመር ። የአሪሞንዲም ብርጌድ ብትንትኑ ወጣ ። በያለበት ሩጫና መበታተን ሆነ ።
“… ምስጋና ይግባውና 7ኛው ባታሊዮን ሶስት መድፎችን አስተርፎ ነበር ። ህይወታችንን ለማዳን እነኚያ ሶስት መድፎች እኩል ሰዓት ያህል እንደተተኮሱ በአበሾች እጅ ወደቁ ። … ለደጀን የተቀመጠው 13ኛውና 3ኛው ብርጌድ ባንድነት ሆኖ ደረሰልን ። ደህና አድርጎ በአዲስ ጉልበት መዋጋት ሲጀምር ልክ 4 ሰዓት ተኩል ሲሆን ከአበሾቹ ጦር … ፈረሰኛ መጣና ወረረው ። ከዚያ በኃላ የኛ ወታደሮች ፀጥ አሉ ። በሠፈራችንም ፀጥታ ነገሰ ። … ” በማለት በሰፊው ፅፏል ።
ረፋዱ ላይ ጀነራል ባራቲየሪ ተማረከ ። ጀነራል ባራቲየሪ በኃላ ላይ ተለቆ አገሩ ከገባ በኃላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቶ ነበር ። ” … ጀነራል አሪሞንዲ ጉልበቱን ተመትቶ ወደቀ ። ኢትዮጵያውያን ሊማርኩት ሲመጡ በጎራዴው እየተከላከለ አልማረክም ቢል ገደሉት ። እኛ የሰለጠነው አለም ስልጡን ወታደሮች ፥ ምንም አያውቁም ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ ። አበሾች ለባሩድና ጥይት ይሳሳሉ ። የሚገድሉ ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም ። ለዚያውም ቢሆን አስርና 15 ያርድ ያህል ቀርበው በአንድ ጥይት ደራርበው መግደል ይፈልጋሉ ። ያለዚያ ተደባልቀው በጎራዴ መምታትን ይመርጣሉ እንጂ ጥይት ማበላሸት አይወዱም ። ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለሚያባክነው ለሰለጠነው ሀገር ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው ። ለምሳሌ ደጀን የነበረው የመድፈኛው አዛዥ ካፒቴን ፍራንዚኒ መድፎቹን ይዞ ከጦር ሜዳ እንዲገባ ታዘዘ ። 30 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ ከጦሩ ሜዳው ገባ ። ቦታውን አመቻችቶ አንድ የመድፍ ጥይት ገና እንዳስተኮሰ ተገደለ ። ይህም ሊሆን የቻለው ያቺን የመድፍ ጥይት ድምፅ የሰሙ ኢትዮጵያውያን በንዴት ተሞልተው በብዛት ሆነው ስለወረሩት ነው ። የተመካንባቸው ፥ ደጀን የነበሩት መድፎቻችንም ካንድ ጥይት ተኩስ በኃላ ተማረኩ ። … ” በማለት መግለጫውን ሰጥቷል ።
ካፒቴን ሞልቴዶ በፃፈው ደግሞ ” … ከአራተኛ ባታሊዮን አንድ የሸሸ የሱማሌ ወታደር ወደካምፓችን ሲሮጥ መጣ ። ካለሁበት በራፍ ላይ ሲደርስም ወደቀ ። የኛ ጦር ደጀን ነበር ። በአረብኛ ቋንቋም ነገሩ ምንድነው ? ምን ሆንክ አልኩት ። አለቁ ፥ ሞቱ አለኝ ። የወታደሩ ጠርቡሽ (ባርኔጣው) ካጠገቡ ወድቋል ። ጠርቡሹን አቧራና ላብ በክሎታል ። ኮቱ የመድፈኞች ኮት መሆኑን ባውቅም ፥ ምልክት ያለበት የኮቱ እጅጌ ተገንጥሎ ስለሌለ ከየትኛው መድፈኛ ክፍል እንደሆነ ላውቅ አልቻልኩም ። በዚያ ክንዱ ላይ ክፉኛ ስለቆሰለ ደሙ በብዛት ይወርዳል ። ዙሪያውን ከብበን በጥያቄ አጣደፍነው ። አንጌራ ፥ ማንፍሬዲኒ ፥ ቶዜሊ ፥ አስካላ እያለ ይቃዣል ።
“ምንድነው የምትለው ! አልኩት
“ሰላም መቶ አለቃ ። አበሾች ደርሰዋል ፥ እዚህ ናቸው ። የአራተኛው ወታደር ሁሉ አለቀ ። ሁሉም ሞቱ ። ማጆር ቶዚሊ ሞተ ። አንጊራ ሞተ ። ማንፍሬዲኒ ሞተ ። ሁሉም ፥ ሁሉም ሞቱ አለኝ ።
“ንገረን እንዴት ሞቱ ? አልኩት ።
” ዛሬ ጧት ። አበሾቹ ብዙ ነበሩ ። ግማሹ ያህል ሞተ ። ሌሎቹ ግን መጡብን ። መድፍ ይተኮሳል ። ጥይት ይተኮሳል ።አበሾቹ ግን መጡብን ። ኦህ ስንትና ስንት መሰሉህ ።
“በማን ውስጥ ነበርክ ? አልኩት ።
“ማንፍሬዲኒ ውስጥ ።
“አይተሀል እሱን ?
“አዎን አይቼዋለሁ ፥ ሞቷል ።
“አስካላንስ አይተኸዋል ?
“አዎን አይቼዋለሁ ፥ ሞቷል (አስካላ ግን ቆስሎ ተማርኳል) ሁሉንም አይቻለሁ ። ሁሉም ሞተዋል ። ታመልጡ እንደሆነ እናንተም አምልጡ ። አበሾቹ ከኃላዬ ናቸው ። ጥፉ አለን የሱማሌው ወታደር ። … ” ሲል ፅፏል።
ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃን።
“…እኛ እንሰናበት እንሰናበት … ” እያልኩ በካስማሰ ዜማ ተሰናበትኳችሁ። ሰናይ ጊዜ።
Article By: Semalign Tadele