ዛሬ ቀን ስንት ነበር? እ ተውት በቃ አትንገሩኝ። መጣልኝ አሁን። 15 ነው ቀኑ ዛሬ ፣ የካቲት 15። የአድዋ ድል መታሰቢያ ሊከበር 8 ቀናት ቀርተውታል።አድዋ ተራራ ብቻ አይደለም፤አድዋ ከተማ ብቻ አይደለም፤አድዋ የቀድሞው መሪ መለስ ዜናዊ የትውልድ ስፍራ ብቻ አይደለም። አድዋ የነፃነት ቀንዲል ነው፣ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን፣ለአፍሪካውያንም ብቻ ሳይሆን፣ለጥቁሮችም ብቻ ሳይሆን፣በመላው አለም ላሉ ጭቁኖች ሁሉ እንጂ፣ለተገፉ እና ለተበደሉ ወገኖች ሁሉ እንጂ። ዛሬ ግን ሀሳቤ ስለ አድዋ ለመዘከር አይደለም። ቀኑ ሲደርስ ዘክርለታለው።ለአሁን ግን ከአድዋ ጦርነት 2 ወራትን አስቀድሞ ስለተፈጠረ ክስተት ላነሳ ወደድኩ።እነሆኝ ተከታተሉኝ።
ነገሩ እንዲህ ነው። የኢጣልያ ዋነኛ ጦር አዲግራት ላይ ሰፉሯል።አንዱ ክፍለጦራቸው ግን መቀሌ ላይ መሽጓል። ሚኒሊክ መቀሌ ላይ የመሸገውን የኢጣልያን ጦር በአንድ ክፍለጦራቸው አስከብበው የቀረውን ጦራቸውን እየመሩ ወደ ወደ አዲግራት ማለፍ ቢችሉም እንዲህ ለማድረግ አልተቻኮሉም። መንገዳቸውን ሙሉ በሙሉ እያጣሩ መጓዝን መርጠዋል። አንድ የሚኒሊክ ወታደር በቅሎ ደንብራበት ወደ ጣሊያን ምሽግ ስታመራበት ወታደሩም ከኋላዋ ሲሮጥ ጣሊያኖች አይተው በመድፍ ያጣድፉታል። እሔን ያዩ ሚኒሊክም “እነዚህ ኢጣልያኖችን ከጉርጓዳቸው ሳላስወጣቸው ወደ ቀኝም ወደ ግራም አልሔድም” ብለው ዛቱ። ወዲያው ምሽጉን አስከብበው በመድፍ እንዲደበደብ አዘዙ።
የሚኒልክን ትዕዛዝ በመከተል ሊቀ መንኳስ አባተ ከጦራቸው ጋር ከምሽጉ በስተግራ ፣ በጅሮንድ ባልቻ በስተቀኝ ሆነው መድፍና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣሊያኖቹ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ምሽጋቸው መቅረባቸውን ሲረዱ መድፍ ለቀቁባቸው። አልሞ ተኳሾቹ እነ ሊቀ መንኳስም አፀፌታቸውን መለሱ።በመድፍ መታኮሱ ቀጠለ። ሊቀ መንኳስ የተኮሱት መድፍ በመስኮት ገብቶ የአንዱን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣሊያኖች ከአንዱ መድፋቸው ጪስ እየተግተለተለ ሲወጣ ሲያዩ ሊቀ መንኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ ላይ ጥይት እንደ በረዶ አዘነቡባቸው። ግን አንድ ሰውም አልተጎዳም።
መታኮሱ ቀጠለ። ይህን የተመለከቱት እቴጌ ጣይቱ አንድ ሀሳብ አመነጩ። አጠገባቸው ቆሞ ወደ ነበረው አዛዥ ዘሚካኤል ዞረው ” ሂድና ከሊቀ መንኳስ ጋር እየተመካከርክ ምንጩን መያዝ ትችል እንደሆነ ሞክር” አሉት። ሊቀ መንኳስ መልዕክቱ እንደደረሳቸው ምንም እንኳ ምንጩ ለጣሊያን ምሽግ ቢቀርብም መተላለፊያውን በመድፍ እያስጠበቁ ለሊት ወታደሮቻቸውን ልከው ምንጩን ማስያዝ እንደሚችሉ ላይ አረጋገጡላቸው።ይህ ሀሳብ ለሚኒሊክ ቀረቦላቸው መልካም ነው ሲሉ ፍቃዳቸውን ሰጡ። እቴጌ ጣይቱ ወታደሮቻቸውን ጠርተው እንዲህ ሲሉ አዘዟቸው።
” እስካሁን ድረስ እምሽጉ ውስጥ ገብተን ለመዋጋት ደስታችን ነው ትሉ ነበር። ነገር ግን ወደምሽጉ ገብቶ ለመዋጋት እንደዚህ ለበዛችሁት ጦር የምሽጉ መንገድ ጠባብ ስለሆነ ከኢጣልያኖች መድፍና ጥይት የበለጠ እርስ በእርሳችሁ ትገዳደላላችሁ። ስለዚህ ሄዳችሁ ኢጣልያኖቹ ውሀ እንዳይቀዱ ምንጩን ጠብቁ። እናንተ እስካሁን እምሽግ ገብተን እንዋጋለን የምትሉት የሜዳን ጦርነት እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ። በዚህ ጦርነት ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ለሞቱም ተዝካራቸውን አወጣላቸዋለሁ፤ልጆቻቸውንም እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን”
ገብረጊዮርጊስ ድልነሴ እና ሸዋዬ የተባሉ ሶስት ጎበዛዝት አሽከሮች በስራቸው ሶስት ሶስት መቶ ባለ ባለጠመንጃ ወታደር ይዘው ወደ ምንጩ ወረዱ። ኢጣሊያኖች ምንጩ ለምሽጋቸው በጣም የቀረበ ስለነበር ኢትዮጵያውን በዚያ በኩል ይመጡብናል ብለው አልገመቱም ነበር። ልክ ኢትዮጵያዊያኑን ሲያዩ መድፋቸውን እየጎተቱ አምጥተው ተኩስ ከፈቱባቸው። ቀውጢ ውጊያ ሆነ።እነ ገብረ ጊዮርጊስ ጠንክረው በመዋጋታቸው ጣልያኖቹ ወደ ምሽጋቸው መመለስ ግድ ሆነባቸው። ምሽጋቸውን ተመልሰው አዲስ የውሀ አጠቃቀም ህግ አረቀቁ፤ያላቸውን ውሀ በቁጠባ ለመጠቀም እንዲያመቻቸው። ግን ቀናት በሔዱ ቁጥር የውሀ ጥም ከአቅማቸው በላይ ሆነባቸው።
የኃላ ኃላ አደራዳሪዎች በመሀል ገብተው በከበባና በውሀ ጥም እየተሰቃዩ ያሉ ጣሊያኖች የመቀሌን ምሽግ ለቀው እንዲወጡና ወደ አዲግራት እንዲመለሱ ፣ ኢትዮጵያውያንም እንዳይወጓቸው አስማሟቸው። ጣሊያኖቹ ነጭ ባንዲራ እያውለበለቡ ምሽጉን ለቀው ወጡ። ኢትዮጵያውያኑም ሳይተናኮሏቸው በዝምታ አሳለፏቸው። የየከፋ ደም መፋሰስ ሳይፈጠር ቀረ። ይህ ድርድር ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ ነበር። ኢጣልያ በረሀብና በውሀ ጥም ሊያልቅ የነበረ አንድ ክፍለ ጦር ከነመሳሪው መልሳ አግኝታለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ የትግራይ ዋና ከተማ የሆነውንና የአፄ ዮሀንስ ቤተመንግስት የሚገኝበትን መቀሌን አስለቅቆ ጠላትን እስከ አዲግራት መግፋት ከአላጌ ጦርነት ወዲህ ያገኘችው ሁለተኛ ድልዋ ሆኖ ተቆጥሮላታል።
የዛሬ ፅሁፌ አላማዬም ይህ ነው። እቴጌ ጣይቱን መዘከር። ብልህነት ከጀግንነት እኩል ክብር ይገባዋል። ብዙ ጊዜ ወንዶች በጡንቻችን እናስባለን። ሁሉም ነገር በሀይልና በጉልበት ሚፈታ ይመስለናል። ግን አይደለም። ቢሆንም እንኳ ብዙ ዋጋ አስከፍሎን ነው። ስለዚህ ትንሽ ብልጠት ወይም ብልሀት ያሻናል። ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ ከወንዶች በተሻለ ብልህ ናቸው። በምንሰራው በእያንዳንዱ ስራ ሴቶችን ብናማክርና ብናካትት ካሰብንበት የማንደርስበት አንዳች ምክንያት የለም። በተለይ ፖለቲከኞች አስቡበት።
Article By: Semalign Tadele
It is an amazing article that empowers women and also celebrates the victory of Adwa.