አድዋ እና ኪነ ጥበብ
|
ታመነ መንግስቴ
|
ታሪክ
ራሱ የአድዋ ድል የጥቁር ግስላ ህዝብ ደማቅ ጥበብ ነው። ንጉሱ እምየ ምኒልክ ከጥበባቸውና ለእውቀት ካላቸው ጉጉት የተነሳ የሚወዱት የሚወዳቸው የዘመኑ ህዝብ “ምኒልክ ሰይጣን ነው ልቤ ጠረጠረ” እስከማለት ደርሷል። ያንን እብሪተኛ የጣልያን ጦርም ኢትዮጵያዊያን ጥጋቡን ሲያስተነፍሱለት እየፎከሩ፣እየሸለሉ፣ፋኖ-“ፋኖ እያሉ ነበር። ከጦር ሜዳ አርበኞች ጎን ተሰልፈው ግፋ የሚሉት አዝማሪዎች-የፈራውን ወታደር እያደፋፈሩ፣የደፈረውን በተከሸነ ግጥም እያሰማመሩ አድዋን አድዋ አደረጓት።
“አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት።”
ጥበብን ከምንጩ የቀዳቻት ረቂቅ ዘፋኝ እጅጋየሁ ሽባባው በሚነሽጥ የዜማ ቅላፄ ስትለው አድዋ ኢትዮጵያዊያንና ለብዙ መቶ ዓመታት ባህር አቋርጠው እንደ እቃ ሲሸጡ ለነበሩ ጥቁር አፍሪካዊያን የዛሬ ኩራት ትናንት ደግሞ “መቼ ተነሱና የወዳደቁት” ያለቻቸው ኢትዮጵያዊያን የደምና የአጥንት ግብር የተከፈለባት ደማቅ ድል መሆኗል ታወሳለች—እጅጋየሁ ሽባባው—ትናገር አድዋ።
የዘመናችን የሙዚቃው ንግስት እጅጋየሁ ሽባባው፦
“የተሠጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል በደምና በአጥንት።”
ማለቷ ያ ታላቅ የጥቁር ህዝቦች ድል በኢትዮጵያዊ የገበሬ ጦር መስዋዕትነት የተገኘ እንጅ በተራቀቀ የጦር መሳሪያ፣በሰለጠነ ጥቂት ወታደር የተጠናቀቀ አለመሆኑን ይገልፃል። በጦርነቱ ወቅት ጣሊያን ሃያ ሺህ ወታደሮችንና የዘመኑ ጠብ መንጃዎችን ስታቀርብ ኢትዮጵያ ደግሞ አምስት እጥፍ ማለትም ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የገበሬ ጦር እና እዚህ ግባ የማይባል መሳሪያ ይዛ ነበር። ስለዚህ ጥቁሩ ግስላ ጦር ያሸነፈው በብዛቱ እና በአምላኩ ተራድኦ ደሙን ወደ መረብና ተከዜ ወንዞች አፍሶ-አጥንቱን በአድዋ ተራሮች ላይ ከስክሶ ነበር-ለዚያ ነው እሷ፦”ሰው ተከፍሎበታል በደምና በአጥንት”ማለቷ።
ሳልሳዊ ቴዎድሮስ-ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ(ቴዲ አፍሮ) “ጥቁር ሰው” በሚለው ደማቅ አልበሙ ላይ “ኑ አድዋ ላይ እንክተት” ሲል ይጀምርና፦
“ኑ አድዋ ላይ እንክተት ያ የጥቁር ንጉስ አለና
የወኔው እሳት ነደደ ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና።”
እያለ ታላቁ ንጉስ አፄ ምኒልክ መስከረም ሰባት ቀን ሺህ 888 ዓ.ም እንጦጦ ማርያም ሆነው “እምየ” ለሚላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ—“ድንበር የሚገፋ፣ኃይማኖት የሚያጠፋ-ተወኝ ብለው እያደር እንደ ፍልፈል አፈር የሚገፋ ጠላት መጥቷልና የአገሬ ሰው እስከ ዛሬ ያስከፋሁህ አይመስለኝም፤እኔንም አስከፍተኸኝ አታውቅምና ዘመቻየ በየካቲት ስለሆነ —እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።” አሉትና የአገር ጉዳይ በጣም ለሚገባው-“ለአገርህ ስትል”ብለው፣ትዳሩ ለሚያባባው በሚስቱ አባብለው፣ኃይማኖቱን ለሚወዳት “ወስልተህ የቀረህ ማርያምን አልምርህም” የምትል መሃላ ምለው ጥቁሩ ንጉስ እምየ ምኒልክ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘን ለቁጥር የታከተ ጦር አዘመቱ፦
“አድዋ ሲሄድ ምኒልክ ኑ ካለ
አይቀርም በማርያም ስለማለ።”
ይቀጥላል የዘፈኑ ንጉስ ቴዲ አፍሮ፦
“አባቴ ምኒልክ ድል አርጎ ሰራው የእኔን ልክ
ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳዬ ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ
አባቴ ወኔውን ተኮሰው ምኒልክ ጥቁር ሰው።”
ይሄ ግጥም ጣዕሙ ልዩ ነው። “አባቴ ምኒልክ ድል አርጎ ሰራው የእኔን ልክ” ያለበት አገላለፅ ያረካል። አንድ ኢትዮጵያዊ በደሙ ውስጥ የድል፣የአሸናፊነት ውህድ ተጨምሮበት ይወለዳል።ከአድዋ ድል በሗላ ኢትዮጵያዊያን ማሸነፍ መክሊታቸው ሆነ-ከጦር ሜዳ ባሻገር በስፖርቱ ሜዳ ሻምበል አበበ ቢቄላ በሮም ጎዳናዎች ያለ ጫማ ሮጦ ዳግም የጥቁርን ህዝብ ሃያልነት አስመሰከረ-ሺህ አለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ የማይመስሉ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮችን -ክብረ ወሰኖችን እየቀለጣጠመ ጥቁር ህዝብ በተለይም ኢትዮጵያዊ ለማሸነፍ የተፈጠረ እስኪመስል አስጠረጠረ—አድዋ እና ምኒልክ—ድል አርገው ሰሩት የእኛን ልክ።
አሁንም ቴዲ አፍሮ በማይነጥፍ ብዕሩ ግጥም አዋቅሮ፣በምጡቅ ምናቡ ዜማ ቀምሮ አድዋን ሲዘፍነው ለጉድ ነው።
“ዳኘው ያሉት አባ መላ ፊት ሃብቴ ዲነግዴ
ሰልፉን በጦር አሰመረው ፊት ሆኖ በዘዴ።”
ዳኘው ያላቸው አፄ ምኒልክን በፈረስ ስማቸው ሲጠራቸው ነው። አባ ዳኘው ፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን ከብልጠታቸው፣ከብልሃታቸው ብዛት የተነሳ ይደነቁባቸው ስለ ነበር “አባ መላ”ሲሉ የፈረስም የቅፅልም ስም ሰጧቸው። ቴዲ አፍሮ ለቤት መምቻነት እንዲመቸው”ፊት ሃብቴ ዲነግዴ “ያላቸው እሳቸውን ነው።መቼስ ዘዴኛ የጦር መሪ ነበሩ እና ሰልፉን በጦር አስምረው ጦሩን ከፊት ሆነው በዘዴ መሩት ይለናል ሳልሳዊ ቴዎድሮስ—ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ።
ቴዲ አፍሮ “ወይ ሳልለው ብቀር ያኔ እኔን አልሆንም ነበር እኔ”ሲል የአባቶቻችንን ለንጉሳቸው እሽ ብሎ መዝመት ከዛሬው ንፁህ ኢትዮጵያዊ ማንነት አንፃር አይቶት ይመፃደቃል—እውነትም የዚያን ጊዜው ኢትዮጵያዊ በንጉሱ ላይ አምፆ አድዋ ሳይዘምት ቢቀር ኖሮ እንጀራን ፓስታ—አክሱም ፅዮንን ቫቲካን—ቴዎድሮስ ካሳሁንን ዲ ቦኖ በሚል መጠሪያ እናገኛቸው ነበር—አድዋ ብዙ ነገር የሆነች ታላቅ ድል።
ኢጆሌ ቢያኮ-የአገሬ ልጆች እያለ በኦሮምኛ ቃላት ግጥሙን የከሸነው ቴዲ አፍሮ እቴጌ ጣይቱ የኢትዮጵያ ብርሃንንም በሚጠቅስበት ገፁ ላይ፦
“የቀፎ ንብ ሲቆጣ ስሜቱ ከፊት ሆና መራችው ንግስቱ”
እያለ ያችን የድል ቀንዲል ገና የውጫሌ ስምምነት መበላሸቱን ስታውቅ አንቶኖሊ የሚባልን የጣልያን ቀዥቃዣ–“እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ነገር ግን የአገሬን ነፃነት የሚጋፋ ውል ከመፈራረም ጦርነትን እመርጣለሁና የዛሬ ሳምንት ና እንጠብቅሃለን። “እንዳለችው በአድዋ ተራሮች ላይ ከባለቤቷ ንጉስ ምኒልክ ጎን ሶስት ሺህ ጦሯን እየመራች ጠላቷን አፈር ድሜ አበላችው። “የቀፎ ንብ ሲቆጣ ስሜቱ ከፊት ሆና መራችው ንግስቱ።”
አድዋ እንድያ ሆነች።ተሸላሚው(ሎሬቱ) ፀጋየ ገብረ መድህን አፈሩ ይቅለለውና፦
“ዋ …አድዋ !…
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው በለው
ዋ …አድዋ …”እያለ የተቀኘላት የጥቁር ህዝብ ደማቅ ድል በአንድ ጀምበር የወራሪውን የጣሊያን ጦር ውሃ ውሃ አስብላ ውሃ አድርጋው ቀረች። አድዋ—የአፍሪካዊነት ድል አርማ።
ፊታውራሪ ገበየሁ ወይም አባ ጎራው—የአምባላጌ የሚባለውን በእግር ኳስ ቋንቋ ለአድዋው የፍፃሜ ፍልሚያ ግማሽ ፍፃሜ የነበረውን በድል ያጠናቀቁ የፊትመስመር አጥቂ ነበሩ። አድዋ ላይም፦
“የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው።”
ተብለው ሲዋጉ የሞቱ እንደሁ ሬሳቸው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ሸዋ መጥቶ ሊቀበር-ሲሸሹ ጀርባቸውን የተመቱ እንደሁ የአሞራ እራት ሆኖ ሊቀር ከምኒልክ ጋር ተማምለው ከጣሊያን ጋር ፊት ለፊት ሲዋጉ ተመተው ወደቁ። በቃላቸው መሠረት እምየ ምኒልክ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር አስከሬናቸውን አስጭነው አንጎላ ኪዳነ ምህረት በተባለችው የሰሜን ሸዋ ደብር አስቀበሯቸው። አዝማሪውም ሌላ ጀግና ሊያጀግን አስቦ፦
“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።”
ብሎ ባልቻ ሳፎን በፈረስ ስማቸው ባልቻ አባ ነፍሶን የመድፍ ዘዋሪ አድርጓቸው ዋለ።
“በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው በለው”
እንዲል ሎሬቱ።
ኢትዮጵያዊያንን ከያሉበት በአንድ ነጋሪት፣በአንዲት የክተት አዋጅ ተጠራርተው ደማቅ ታሪክ የፃፉበት ያ_ድል በጠቢባን ዓይን እንዲህ ታይቷል።
ቢሆንም ገና ብዙ ጦማር፣ብዙ ቅኔ፣አዕላፍ ዜማና መዓት ግጥም ይቀራል፤አገር በኪነት ካለበት ከፍታ በላይ ከፍ ብሎ ይሰራል!
ይቆየን!
Article By: Tamene Mengste